Sunday, May 10, 2015

ድር ድሮ የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች ከአሜሪካን ነበር ወደ ኢትዮጵያ የሚጎርፉት። አሁን አሁን ደግሞ የተቸገርነው እኛ የሰለቸንን የብልጽግና ወንጌል ከኢትዮጵያ ተጋብዘው የሚመጡት ሰባኪዎች አይናቸውን በጨው አጥበው ሊሰብኩን መዳፈራቸው ነው። የኢትዮጵያ አብያተ ክርስትያናት ህብረት ይህንን ትምህርት ካወገዘች እንኳን አመታት አልፈውል። እንዴት ነው ነገሩ። አሁንማ በመድረክ ላይ ቆመው የገንዘብ መላክያ ፖስታ እያውለበለቡ አትለፉኝ ማለት የቀራቸውንም ማየት ጀምረናል። አልፈው አይን ሲያወጡም የዲያስፖራ  ምእመን አይን አውጥተህ ካለመንክ አይሰጥም ብለው መናገርም  ጀምረዋል። ይመስለኛል የብልጽግና ተኮር ሰባኪዎችን የገንዘብ አሰባሰብ ዘዴ (ድሮ በአለም እያለን በአራዳ ቋንቋ ፈለጣ ነበር የሚባለው)  ለጥቂት ጥቅም መልካም ነው በማለት የዋሆቹ እያዳቀሉት ይመስለኛል። አዲስአበባዎች አደብ ግዙ እንጂ።  እረ ወንጌልንና መልካም አስተማሪዎቻችሁን  አታሰነቅፉ።  እስቲ  የአዲስ አመት ኮንፍረነስ ለመካፈል ቤተክርስቲያን ሄደው አንዳንዶች የታዘቡትን ከፌስቡክ ላይ በተስፋዬ ተሰማ የተጻፈውን እናስነብባችሁ።

ትላንት ማታ የአዲስ አመት ኮንፍረነስ ለመካፈል ቤተክርስቲያን ሄጀ ነበር። ከኢትዮጵያ የተጋበዘው ሰባኪ የሚያስተምረው ስለእምነት ነበር። በርግጥ ይሄ ትምህርት የሰባኪው የራሱ ትምህርት አይደለም። የዚህ አይነቱ የእምነት ትምህርት አዲስ የመጣ እና ብዙ መፅሀፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ነገሮች የታጨቁበት የዘመኑ ብልጣብልጥ ሰባኪያን በአለም ዙሪያ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚጠቀሙበት፤ የኛ ሀገር ሰባኪወች ደግሞ የዚህ ጥቅም ተጋሪ ለመሆን የሚያራግቡት ትምህርት ነው ተበሎ በብዙ የሰነ መለኮት ምሁራን እና ክርስቲያኖች ይታመናል።
ተጋባዡ ሰባኪ የሚሰብከውን የእምነት ትምህርት ያጠናክርልኛል ብሎ የተለያዩ የመፅሀፍ ቅዱስ እና የሳይንስ ምሳሌዎችን እንግሊዝኛ እየቀየጠ ቢያስተምርም በመንፈሳዊዉም ሆነ በሳይንስ ጉዳዮች ዙሪያ ያነሳቸው ነጥቦች ግራ የሚያጋቡና እርስ በርስ የሚጣረሱ ሆነውብኝ ከቤተክርስቲያን ወጣሁ።
በስብከቱ ላይ ብዙ አደናጋሪ መልእክቶች በመተላለፉቸው ሁሉንም አንስቼ ስለማልዘልቅ ከተናገራቸው አይነተ ብዙ ስህቶች አንድ ከመንፈሳዊ አንድ ከሳይንሳዊ ስህተቶች ቀንጭቤ ልናገር። ሰባኪው አሰተምርበታለሁ ያለው ርእስ የእምነት ህጎች የሚል ነው።እንደ ሰባኪው አባባል “እኛ የእግዚአብሄር ልጆች ነን፣ የምንኖረው በአዲስ ኪዳን ዘመን ነው፣ በጌታ ካመንን ስራ ሳንሰራ እንበለፅጋለን፤ ስራ መስራት እርግማን ነው ደግሞም የብሉይ ኪዳን ህግ ነው።”
ሰባኪው በተጨማሪም “እስካሁን ያልበለፀግነው ስለማናምን እና ያመነውን ነገር ስለማንናገር ነው። ገንዘብ ለፖስተሮች እና ለቤተክርስቲያን አለመስጠታችንም ሌላው በድህነት የመኖራችን ምክንያት ነው” ይለናል።፡መልእክቱ ባጠቃላይ ስራ አትስሩ ገንዘብ አምጡ ነው።
ስለ እግዚአብሄር በረከት፣ ተግቶ ስለመስራት እና ሰለመበልፀግ መፅሀፍ ቅዱስ በበርካታ ክፍሎች የሚናገረው እውነት ግን ሰባኪው ካለው ነገር ጋር ፍፁም ተቃራኒ ነው።፡በርግጥ እኛ የግዚአብሄር ልጆች ነን። እግዚአብሄር ሰውን ይባርካል። ነገር ግን ሰው የሚባረከው ቢሊየነር ነኝ ብሎ ሰለጮኸ እና ሰለ ፎከረ አይደለም።፡ይህን ትምህርት የሚያሰተምሩት ሰወች ለምን እናንተ ቢሊየነር አትሆኑም ተብለው ሲጠየቁ በእምነት አርግዘናል ይላሉ መቸ እንደሚወልዱትም አይታወቅም።
ሰው የሚባረከው ያለፅድቅ በሆነ ባዶ ፋከራ ሳይሆን የእግዚአብሄርን ፅድቅ በመፈለግ እና በስራ ነው። ሰባኪው እንደሚለው ሰራ መስራት እርግማንና የብሉይ ኪዳን ህግ ብቻም አይደለም።፡ከአዲስ ኪዳን 27 መፅሀፍት 13ቱን የፃፈው ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሄር ልጆች ለሆንን ክርስቲያኖች በ2ኛ ተሰሎንቄ ምእራፍ 3: ከቁጥር 8 እሰከ 13 ላይ ” ከናንተ ዘንድ በአንድስ እንኩዋን እንዳንከብድበት ሌሊት እና ቀን በድካም እና በጥረት አየሰራን እንኖር ነበር,…..ደግሞም ከናንተ ጋር ሳለን ሊሰራ የማይወድ አይብላ ብለን አዘናችሁ ነበር” በማለት ክርስቲያኖች ሰራ እንዲሰሩ ግድ ብሎአል።
ቅዱስ ጳውሎስ የሰራ ጠቃሚነት በቃል ብቻ ሳይሆን በራሱ የግል ህይወትም ድንካን እየሰፋ ወንጌልን በመስበክ በተግባር ያስመከረ ታላቅ ሀዋርያ ነበር። የፕሮቴስታንት ሀይማኖትን ታሪክ ስናጠና ሀይማኖቱ ገና ከመነሻው ጠንካራ የስራ ባህልን እንደምነቱ አካል የሚወስድ፤ ተግቶ መስራት ለግለሰብ እና ለማህረሰብ ብልፅግና መሰረት ነው ብሎ የሚያምን ነው። የማህበረሰብ እና የታሪክ አጥኝወች በግልፅ እንዳስቀመጡት የአሜሪካ እና የአውሮፓ ብልፅግና ዋና ምክንያት የፕሮቴስታንት ሀይማኖት የሰራ ባህል ነው።
ይህ ሰባኪ እና መሰል የብልፅግና አስተማሪዎች የተገለጠውን የእግዚአብሄር ቃል እውነት በማጣመም የሀይማኖት አባቶች በህይወት ያሳዩንን ምሳሌ ችላ ብለው ሰራ አትስሩ ገንዘብ አምጡ በማለት ህዝቡን ግራ ያጋባሉ፤ ሰውን በቀቢፀ ተስፋም ይሞላሉ። ሰባኪው በሳይንስ ዙሪያ ሰለሚያስተምራቸወ ታላላቅ ግድፈቶች እና በጉባኤው ውስጥ ተቀምጠው ያዳምጡ ሰለነበሩ ሳይንቲስቶች አስተያየት በሚቀጥለው ፅሁፌ ለመፃፍ እሞክራለሁ።
“እውነትን ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችሁዋል”
እባካችሁ የእውነትን ወንጌል የሚሰብኩትን እንደግፍ!!

No comments:

Post a Comment