Sunday, October 2, 2016

ሰባቱ የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች ልዩ ምልክት

wolf-in-sheeps-clothing orginal
እግዚአብሔርን እንዲያውቁ በግልጥ ይናገራሉ፥ ዳሩ ግን የሚያስጸይፉና የማይታዘዙ ለበጎ ሥራም ሁሉ የማይበቁ ስለ ሆኑ፥በሥራቸው ይክዱታል።” ቲቶ 1:16

በሃይማኖት ብትኖሩ ራሳችሁን መርምሩ፤ ራሳችሁን ፈትኑ::” ቆሮ 13:5
ዛሬ እየኖርንበት ባለንበት አለም በዘመን ፍጻሜ የመጨረሻው አስራ አንደኛው ሰአት ላይ እንደምንገኝ ሁላችንም እናምናለን በተለይ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች ዘመኑ የጭንቅ እና የመከራ ዘመን እንደሆነ እንዲሁም አያሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉ የትንቢት ቃሎች አብዛኞቹ የተፈጸሙ ሲሆን ቀሪዎቹ እና ጥቂቶቹ ደግሞ በፍጥነት በመፈጸም ላይ እንዳሉ ሁላችንም ከሞላ ጎደል እናውቃለን። ዛሬዛሬ እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል እና በግልጽ በየቤተክርስትያኑ እንደሚታየው እግዚያብሔርን የማምለክ እና የማስመለክ ስርአት ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ ይዘው የሚገኙት የቤተእምነቱ ባለቤቶች እና መሪዎች( ሐዋሪያቶች፣ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች )ከማንም በላይ እና በፊት እንዲሁም ከምንግዜውም በላይ ለገሀነም ደጅ በጣም ቀርበው ይገኛሉ። የእግዚያብሔርም ቃል ስለነዚህ ወደ ፍርድ ስለሚቀርቡት እና በስሙ ስለሚነግዱት ሀሰተኞች እንዲህ በማለት ይናገራል “ፍርድ ከእግዚአብሔር ቤት ተነሥቶ የሚጀመርበት ጊዜ ደርሶአልና፤ አስቀድሞም በእኛ የሚጀመር ከሆነ ለእግዚአብሔር ወንጌል የማይታዘዙ መጨረሻቸው ምን ይሆን? ጻድቅም በጭንቅ የሚድን ከሆነ ዓመፀኛውና ኃጢአተኛው ወዴት ይታይ ዘንድ አለው?” 1 ጴጥ 4:17-18 የእግዚያብሔር እውነተኛ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚመሰክርልን እና እንደሚያስተምረን በዚህ ዘመን እራሳቸውን ከአገልግሎት ዘመን ብዛት እራሳቸው ላይ በእግዚያብሔር ስም የመጠሪያ የስልጣን “ቅቤ” የቀቡ ሀሰተኛ ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እና አስተማሪዎች እግዚያብሔር እንደማያውቃቸው እና እርሱም ለአገልግሎት እንዳልጠራቸው በቅዱስ ቃሉ እንዲህ በማለት ይመሰክርልናል “እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል። ስለዚህ እግዚአብሔር በስሜ ትንቢት ስለሚናገሩ ነቢያት። በዚህች አገር ሰይፍና ራብ አይሆንም ስለሚሉ ስላላክኋቸው ነቢያት እንዲህ ይላል። እነዚያ በሰይፍና በራብ ይጠፋሉ።” ኤር 14፡14_15
“እረኞችንም እንዲህ በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን?ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም።የደከመውን አላጸናችሁትም የታመመውንም አላከማችሁትም የተሰበረውንም አልጠገናችሁትም የባዘነውንም አልመለሳችሁትም የጠፋውንም አልፈለጋችሁትም በኃይልና በጭቈናም ገዛችኋቸው። እረኛንም በማጣት ተበተኑ፥ ለምድርም አራዊት ሁሉ መብል ሆኑ፥ ተበተኑም።በጎቼ በተራሮች ሁሉና በረዘሙ ኮረብቶች ሁሉ ላይ ተቅበዝብዘዋል፥ በጎቼም በምድር ፊት ሁሉ ላይ ተበትነዋል፤ የሚሻም የሚፈልግም አልነበረም። ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እኔ ሕያው ነኝና እረኛ ስለሌለ እረኞቼም በጎቼን ስላልፈለጉ እረኞችም ራሳቸውን እንጂ በጎቼን ስላላሰማሩ፥ በጎቼ ንጥቂያ ሆነዋልና፥ በጎቼም ለምድር አራዊት ሁሉ መብል ሆነዋልና፤ ስለዚህ፥ እረኞች ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በእረኞች ላይ ነኝ፥ በጎቼንም ከእጃቸው እፈልጋለሁ፥ በጎቼንም ከማሰማራት አስተዋቸዋለሁ። ከዚያም ወዲያ እረኞች ራሳቸውን አያሰማሩም፤ በጎቼንም ከአፋቸው አድናለሁ፥ መብልም አይሆኑላቸውም።” ሕዝ 34፡2_10
ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጨረሻው ዘመን ልዩ ምልክት እንደሆነ አጥብቆ ለደቀመዛሙርቶቹ የነገራቸው ሲሆን ለእኛም ደግሞ በክርስቶስ ስም ወንጌል ይዘው የሚነሱ ሀሰተኛ ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች እንደሚነሱ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ አስተምሮናል። “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። ከእሾህ ወይን ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲሁ መልካም ዛፍ ሁሉ መልካም ፍሬ ያደርጋል፥ ክፉም ዛፍ ክፉ ፍሬ ያደርጋል። መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም።” ማቴ 7:15_18
በእግዚያብሔር ጥሪ ተደርጎላችሁ ወደ ክርስቶስ ሙላት ለመድረስ የምትናፍቁ የእግዚያብሔር ቤተሰቦች የተጠራችሁለትን ጥሪ በድል ለመጨረስ እና ከታላቁ ፍርድ ለማምለጥ ግዜው እና ሰአቱ አሁን እንደሆነ አውቃችሁ በመንቃት እያንዳንዱን መንፈሳዊ ህይወታችሁን ከእግዚያብሔር ቃል ጋር በማዛመድ እንዲሁም በተጨማሪ ከዚህ ቀደም በስጋዊ መረዳት ስታደንቋቸው እና ስታሞጉሷቸው የነበሩትን ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እና አስተማሪዎቻችሁን የተገለጠ ፍሬ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት በሰባቱ የእግዚያብሔር ቃል መነጽር ይዩዋቸው። “ራሳችንን ብንመረምር ግን ባልተፈረደብንም ነበር፤ ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኮነን በጌታ እንገሠጻለን።”1 ቆሮ 11:31_32
ሰባቱ የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች ልዩ ምልክት
  1. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች ሁል ግዜ ሰዎችን ለማስደሰት ይተጋሉ፦ ሁል ግዜ የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች የልባቸውን እና የስጋቸውን ፍላጎት በተከታዮቻቸው ጆሮ እንዲጣፍጥ እና እንዲታመን አድርገው በትንቢታዊ ቃል አሽሞንምነው ያቀርባሉ። በተጨማሪም ስለንስሀ ግዜ እና ቅድስና ህይወት አጥብቆ ማስተማር ጉዳያቸው አይደለም። በተቃራኒው እውነተኛ ከእግዚያብሔር የተጠራ አስተማሪ እግዚያብሔርን ለማስደሰት ሁል ግዜ ሲተጋ ቃሉንም ያለምንም ማመቻመች ሰዎች የሚፈልጉትን ሳይሆን እግዚያብሔር የሚፈልገውን ብቻ ያስተምራል ለዚህም የእግዚያብሔር ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ በማለት እውነቱን አጥብቆ ያስተምረናል። “ወንጌልን አደራ ይሰጠን ዘንድ እግዚአብሔር የታመንን ሆነን እንዳገኘን መጠን፥ እንዲሁ እንናገራለን፥ ልባችንን የሚመረምር እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን ደስ እንደምናሰኝ አይደለም።እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጐምጀት አልሠራንም፤የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።ነገር ግን ሞግዚት የራስዋን ልጆች እንደምትከባከብ፥ በመካከላችሁ የዋሆች ሆንን፤እንዲሁም እያፈቀርናችሁ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለማካፈል ብቻ ሳይሆን የገዛ ነፍሳችንን ደግሞ እናካፍላችሁ ዘንድ በጎ ፈቃዳችን ነበረ፥ ለእኛ የተወደዳችሁ ሆናችሁ ነበርና።ወንድሞች ሆይ፥ ድካማችንና ጥረታችን ትዝ ይላችኋልና፤ ከእናንተ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት ሌሊትና ቀን እየሠራን፥ የእግዚአብሔርን ወንጌል ለእናንተ ሰበክን።በእናንተ በምታምኑ ዘንድ በእንዴት ያለ ቅድስናና ጽድቅ ነቀፋም በሌለበት ኑሮ እንደ ሄድን፥ እናንተና እግዚአብሔር ምስክሮች ናችሁ፤ወደ መንግሥቱ ወደ ክብሩም ለጠራችሁ ለእግዚአብሔር እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እየመከርንና እያጸናን እየመሰከርንላችሁም፥ አባት ለልጆቹ እንደሚሆን ለእያንዳንዳችሁ እንደ ሆንን ታውቃላችሁና።” 1ተሰ2፡4_12
  2. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች እንዲሁም ተከታዮቻቸው ምእመና ሁል ግዜ ከእውነተኞቹበእግዚያብሔር አገልጋዮች በክፉ ስራቸው ለንስሀ ህይወት ሲነቀፉ አይወዱምም አይቀበሉምም  የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች እንዲሁም ተከታዮቻቸው ስህተታቸው እና ግድፈታቸው ሲነገራቸው እንዲሁም በይፋ ስለሰሩት ሀጢያት ንስሀ እንዲገቡ ሲጠየቁ በፍጹም የማይቀበሉ ሲሆን በተቃራኒው በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ እንኳ በእግዚያብሔር በራሱ የተመረጡ አገልጋዮች እነ ሙሴ እና አሮን በቅዱሳን ጉባኤ ሲገሰጹ እና ሲነቀፉ ግሳጼውን እና ነቀፌታውን ያለ ምንም ማመቻመች ሲቀበሉ እንዲህ እናነባለን። “በሙሴና በአሮን ላይ ተሰብስበው። ማኅበሩ ሁሉ እያንዳንዳቸው ቅዱሳን ናቸውና፥ እግዚአብሔርም በመካከላቸው ነውና እናንተ እጅግ አብዝታችኋል፤ በእግዚአብሔርም ጉባኤ ላይ ለምን ትታበያላችሁ? አሉ።ሙሴም በሰማ ጊዜ በግምባሩ ወደቀ፤” ዘኁ16፡2_4 የእግዚያብሔር ሐዋርያም ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚህ ዘመን ነቀፌታን ስለማይቀበሉ የሀሰት አገልጋዮች እንዲህ በማለት ያስተምራል። “በመልእክቶቼ የማስደነግጣችሁ አይምሰላችሁ።መልእክቶቹስ ከባድና ኃይለኛ ናቸው፥ ሰውነቱ ግን ሲታይ ደካማ ነው፥ ንግግሩም የተናቀ ነው ይላሉና።እንዲሁ የሚል ይህን ይቁጠረው፤ በሩቅ ሳለን በመልእክታችን በኩል በቃል እንዳለን፥ በፊቱ ደግሞ ሳለን በሥራ እንዲሁ ነን። ራሳቸውን ከሚያመሰግኑ ከአንዳንዶች ጋር ራሳችንን ልንቆጥር ወይም ራሳችንን ልናስተያይ አንደፍርምና፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር ሲያመዛዝኑ፥ ራሳቸውንም ከራሳቸው ጋር ሲያስተያዩ፥ አያስተውሉም።” 2ቆሮ10፡9_12 ሁላችንም ከላይ እንደተመለከትነው የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች እንዲሁም ተከታዮቻቸው ምእመና እውነተኛውን የእግዚያብሔርን ህግ እና ስርአት ሲገለብጡት በግልጽ እንረዳለን።
  3. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች የሚያስተምሩት የራሳቸውን ስጋዊ እውቀት እና ራዕይን ነው፦በነብዩ ኤርምያስ ስለ ዛሬ ግዜ የሀሰት ነብያቶች እና አስተማሪዎች መገለጥ እግዚያብሔር ለነብዩ ኤርምያስ ትንቢታዊ ቃል እንዲህ በማለት ተናግሮት ነበር። “ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ። ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል።” ኤር 14፡14 በዛሬ ግዜ አያሌ ክርስቲያኖች የራሳቸው የሚወዷቸው፣የሚያከብሯቸው፣የሚያመልኩአቸው ፎቶግራፋቸውን የማህበራዊ ሚድያ ገጽ ፕሮፋይል ያደረጉዋቸው የእግዚያብሔር ስም እና ክብር እንዲሁም ህግ እና ስርአቱ ሲጣስ እና ሲረገጥ “ጌታ ይገስጽህ” ከሚል ቀጭን ቃል በላይ የማይወጣቸው የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎቻቸው ስማቸው ገና ሲነሳ ደግሞ አራስ ነብር ስለሚያደርጋቸው የዘመኑ ክርስቲያኖች ቅዱስ ጳውሎስ በትንቢት ቃሉ እንዲህ በማለት አስጠንቅቆ አስተምሮናል። “ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም። ሕይወት የሚገኝበትን ትምህርት የማይታገሡበት ዘመን ይመጣልና፤ ነገር ግን ጆሮቻቸውን የሚያሳክክ ስለ ሆነ፥ እንደ ገዛ ምኞታቸው ለራሳቸው አስተማሪዎችን ያከማቻሉ።እውነትንም ከመስማት ጆሮቻቸውን ይመልሳሉ፥ ወደ ተረትም ፈቀቅ ይላሉ።” 2ጢሞ4፡2_4 ኢየሱስ ክርስቶስም እንደዚህ ያሉትን የሀሰተኞች ልጆችን እንዲህ በማለት ይገስጻቸዋል። “ሰዎች ሁሉ መልካም ሲናገሩላችሁ፥ ወዮላችሁ፤ አባቶቻቸው ለሐሰተኞች ነቢያት እንዲሁ ያደርጉላቸው ነበርና።” ሉቃ 6፡16
  4. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች የሚስቱት አስፈላጊው ትልቁን የእውቀት ቃል ትተውት ትንሹንእና የሚመቻቸውን አንድ ቃል መርጠው በማውጣት በእርሱ ዙሪያ ብቻ በመዞር እየሰነጣጠቁት ያስተምራሉ፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንቢት ቃሉ በዚህ ጊዜ ስለሚነሱት የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች እንዲህ እንዲህ በማለት አጥብቆ ሲያስተምር እና ሲነቅፍ እናነባለን። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር።” ማቴ 23፡23 የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እና አስተማሪዎች በየስፍራዎቻቸው ታላቅ መንፈሳዊ ህግን የመፈጸም ትጋት እንዳላቸው በየመድረኮቻቸው ላይ ይገልጻሉ። ለሚመሩዋቸው ምእመናዎች ትልቁን እና ዋናውን የእግዚያብሔር የህግ ቃል ሳይሆን ትንሹን መርጠው ምእመናዎቻቸው እንዲፈጽሙት በቀጭኑ አስተምረው ያዙዋቸዋል። ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ አስተምሮ እንዲህ በማለት በቅዱስ ቃሉ አስጠንቅቆ አስተምሮናል። “እነዚህን አስተምርና ምከር። ማንም ልዩ ትምህርት የሚያስተምር ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው ጤናማ ቃልና እግዚአብሔርን ለመምሰል በሚስማማ ትምህርት የማይጠጋ ቢሆን፥በትዕቢት ተነፍቶአል አንዳችም አያውቅም፥ ነገር ግን ምርመራን በቃልም መዋጋትን እንደ በሽተኛ ይናፍቃል፤ ከእነዚህም ቅንዓትና ክርክር ስድብም ክፉ አሳብም እርስ በርስ መናደድም ይወጣሉ፥ አእምሮአቸውም በጠፋባቸው እውነትንም በተቀሙ፥ እግዚአብሔርን መምሰል ማትረፊያ የሚሆን በመሰላቸው ሰዎች ይገኛሉ። እንደነዚህ ካሉት ራቅ።ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፥ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል። ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል።መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥ የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ።” 1ጢሞ6፡3_12
  5. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች ሁል ግዜ የስህተት ትምህርታቸውን መጋረጃ እንዲጋርድላቸውየተመረጡ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ጥቅሶችን ይጠቀማሉ፦ ልክ በተለያዩ መዋቢያ ቀለማት እና መአዛው እጅግ በሚያውድ ሽቶ ተጠቅማ ከሌሎች በጣም ጎልታ ለመማረክ እንደምትታይ ሴተኛአዳሪ እንዲሁ የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች ስውር እና አደገኛ የሀሰት ልዩ ልዩ ትምህርታቸውን በተለያዩ አዝናኝ ቋንቋዎች፣በተለያዩ መሳጭ ታሪኮች፣ስላሳለፉዋቸው ትዝታዊ ሀረካቶች፣ስለገጠመኞቻቸው ብዙ ከደኮሰሩ ቡኋላ ማሳረጊያውን ለፕሮግራሙ መጀመሪያ እና መጨረሻ በጥንቃቄ በተመረጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃሎችን በመጠቀም ከሽነው እና አጣፍጠው ይደመድሙታል። ኢየሱስ ክርስቶስ ምን እንደምንሰማ እንድንጠነቀቅ አጥብቆ እንዲህ በማለት አስተምሮናል። “የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም። እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።” ሉቃ 8፡17_18 በተጨማሪም የእግዚያብሔር ሐዋርያም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ነበር ያስተማረው። “ የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን።” 2ቆሮ2፡17 እግዚያብሔርም በሀሰተኛ አስተማሪዎች እንዲሁም ቃሉን በማያነቡ እና በማይመረምሩ እንዲሁም እውነተኛውን እውቀት ለጠሉት ልጆቹ ምሬቱን እንዲህ በማለት ተናግሮዋል። “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል፤ አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ፤ የአምላክህንም ሕግ ረስተሃልና እኔ ደግሞ ልጆችህን እረሳለሁ። እንደ ብዛታቸው መጠን ኃጢአት ሠሩብኝ፤ እኔም ክብራቸውን ወደ ነውር እለውጣለሁ።” ትንቢተ ሆሴ 4:6_7 እንዲሁም በተጨማሪ በዘመኑ ፍጻሜ ሰዎች እውነተኛውን የእግዚያብሔርን ቃል ለመስማት እና ለማግኘት ከየስፍራው ይራወጣሉ ነገር ግን አያገኙም ይላል የእግዚያብሔር ቃል። “እነሆ፥ በምድር ላይ ራብን የምሰድድበት ዘመን ይመጣል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ እርሱም የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም። ከባሕርም እስከ ባሕር ድረስ፥ ከሰሜንም እስከ ምሥራቅ ድረስ ይቅበዘበዛሉ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ለመሻት ይርዋርዋጣሉ፥ አያገኙትምም። በዚያ ቀን መልካካሞች ደናግል ጐበዛዝትም በጥም ይዝላሉ።” አሞ 8:11_13
  6. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች ንዲሁም አስተማሪዎች ሁሌም ፍላጎታቸው የሌሎችን ሀሳቦች ማሸነፍ እና በሀሳቦቻቸውሌሎችን መርዳት እና የተሻሉ ሆነው መገኘትን ሌላው መታወቂያቸው ነው፦ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ግዜ ስለነበሩት የሀይማኖት ሰዎች እንዲሁም በመጨረሻ ዘመን ስለሚከሰቱት የሀሰት ነቢያቶች እና አስተማሪዎች በተከታዮቻቸው ዘንድ ስላላቸው የማሳመን ክህሎት እንዲህ በማለት ነበር ያስተማረው። “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ፥ በሆነም ጊዜ ከእናንተ ይልቅ ሁለት እጥፍ የባሰ የገሃነም ልጅ ስለምታደርጉት፥ ወዮላችሁ።” ማቴ 23፡15 የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች የመጨረሻ አላማቸው በስብከት ስራ የተሻለ እና የተቀናጣ አለማዊ ህይወትን መኖር ብቻ ሳይሆን እንዲሁም በተጨማሪ ከሌላው የተሻለ አሳማኝ ጭንቅላት እንዳላቸው ለማሳየት ተከታዮቻቸውንም ያሸንፋሉ ሁሌም ያሳምናሉ ። ለዚህም ነው እኛም አገር አንዳንድ በደጋፊዎቻቸው እና በተከታዮቻቸው ዘንድ እጅግ ትልቅ ስም ያላቸው የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች ለነሱ የተሻለ የአስተሳሰብ ክህሎት የመሰላቸውን ድርጊት እንዲሁም ከሌሎች በልጠው እና የማስመለክ ፈቃድ ለሰጣቸው መንግስት ቅርበታቸውን እና መወደዳቸውን ለማሳየት በገዛ የስብከት መድረካቸው ላይ ለተከታዮቻቸው የወታደራዊ ጁዶ ማርሻል አርት ትእይንትን ሲያሳዩ በሌላ ግዜ ደግሞ ለህዳሴው ግድብ ገቢ ማስገኛ ታላቅ ወንጌላዊ ሩጫ እና ስብከት ወዘተረፈ…….. ሲደሰኩሩ በግልጽ የምናያቸው።
  7. የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች ተከታዮቻቸውን ያባርራሉ፦ ለዚህም ቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ ስላለው ነገር እንዲህ በማለት እየመከረ አስተምሮናል። “እንግዲህ ክፋትን ሁሉ ተንኰልንም ሁሉ ግብዝነትንም ቅንዓትንም ሐሜትንም ሁሉ አስወግዳችሁ፥ጌታ ቸር መሆኑን ቀምሳችሁ እንደ ሆነ፥ ለመዳን በእርሱ እንድታድጉ አሁን እንደ ተወለዱ ሕፃናት ተንኰል የሌለበትን የቃልን ወተት ተመኙ።” 1ጴጥ2፡1_3 የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች ተከታዮቻቸውን ለምን ከጉባኤያቸው ውስጥ እንደሚያባርሩዋቸው ሲጠየቁ እንዲህ በማለት ይመልሳሉ “እነሱ የዚህን አለም ባለጠግነት እና ክብርን እንዲሁም ቅጥ ያጣ አለመኝነትን ከመጠን በላይ ይሻሉ” እውነት ነው ምን አጠፉ? በዋናዎቻቸው ( የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች )የተሰበኩትን አለማዊ የብልጽግና ወንጌል ነው ተግባራዊ ያደረጉት። በተጨማሪም ከዋኖቻቸው የተገለጠ አለማዊ የህይወት ዘይቤ በማየት እና በመጎምዠት ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በትንቢት ቃሉ እንዲህ ብሎ ነው አስጠንቅቆ ያስተማረው። “ነገር ግን ሐሰተኞች ነቢያት ደግሞ በሕዝቡ መካከል ነበሩ እንዲሁም በመካከላችሁ ደግሞ ሐሰተኞች አስተማሪዎች ይሆናሉ፤ እነርሱም የዋጃቸውን ጌታ እንኳ ክደው የሚፈጥንን ጥፋት በራሳቸው ላይ እየሳቡ የሚያጠፋ ኑፋቄን አሹልከው ያገባሉ፤ ብዙዎችም በመዳራታቸው ይከተሉአቸዋል በእነርሱም ጠንቅ የእውነት መንገድ ይሰደባል። ገንዘብንም በመመኘት በተፈጠረ ነገር ይረቡባችኋል፤ ፍርዳቸውም ከጥንት ጀምሮ አይዘገይም ጥፋታቸውም አያንቀላፋም።” 2ጴጥ2፡1_3 እንዲሁም በተጨማሪ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በትንቢት ቃሉ የሀሰት ሐዋሪያቶች፣ ነቢያቶች እንዲሁም አስተማሪዎች ምንም ነገር እንደማያውቁ እንዲሁም በተጨማሪ ትንቢትም ሆነ የሚያስተምሩት ቃል የገዛ የራሳቸው ቃል እንደሆነ እንዲህ አጥብቆ ያስተምረናል። “ነገር ግን ስለ መተላለፉ ተዘለፈ፤ ቃል የሌለው አህያ በሰው ቃል ተናግሮ የነቢዩን እብድነት አገደ። ድቅድቅ ጨለማ ለዘላለም የተጠበቀላቸው እነዚህ ውኃ የሌለባቸው ምንጮች በዐውሎ ነፋስም የተነዱ ደመናዎች ናቸው።ከንቱና ከመጠን ይልቅ ታላቅ የሆነውን ቃል ይናገራሉና፥ በስሕተትም ከሚኖሩት አሁን የሚያመልጡትን በሥጋ ሴሰኛ ምኞት ያታልላሉ።ራሳቸው የጥፋት ባሪያዎች ሆነው። አርነት ትወጣላችሁ እያሉ ተስፋ ይሰጡአቸዋል፤ ሰው ለተሸነፈበት ለእርሱ ተገዝቶ ባሪያ ነውና።በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት ከዓለም ርኵሰት ካመለጡ በኋላ ዳግመኛ በእርስዋ ተጠላልፈው የተሸነፉ ቢሆኑ፥ ከፊተኛው ኑሮአቸው ይልቅ የኋለኛው የባሰ ሆኖባቸዋል።አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።” 2ጴጥ2፡16_22 ኢየሱስ ክርስቶስም ስለነዚህ በስሙ ስለሚነግዱ ሀሰተኞች መጨረሻቸውን እንደዚህ ነው ያለው። “ስለዚህም ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ። በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም። በዚያ ቀን ብዙዎች። ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፥ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፥ በስምህስ ብዙ ተአምራትን አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም። ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፥ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” ማቴ 7:20_27
  8. እኔም የዛሬው መልእክቴን በነዚህ ሶስት ታላላቅ የእግዚያብሔር ቃሎች በመጠቀም መልእክቴን ቋጭቻለሁ። “የአፌን ቃል ስማ ከእኔም ዘንድ አስጠንቅቃቸው። እኔ ኃጢአተኛውን። በእርግጥ ትሞታለህ ባልሁት ጊዜ፥ አንተም ባታስጠነቅቀው ነፍሱም እንድትድን ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢአተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው፥ ያ ኃጢአተኛ በኃጢአት ይሞታል፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ። ነገር ግን አንተ ኃጢአተኛውን ብታስጠነቅቅ እርሱም ከኃጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፥ በኃጢአቱ ይሞታል፥ አንተ ግን ነፍስህን አድነሃል። ደግሞ ጻድቁ ከጽድቁ ተመልሶ ኃጢአት በሠራ ጊዜ እኔ በፊቱም ዕንቅፋትን ሳደርግ፥ እርሱ ይሞታል፤ አንተም አላስጠነቀቅኸውምና በኃጢአቱ ይሞታል ያደረጋትም ጽድቅ ነገር አትታሰብለትም፤ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ።ነገር ግን ኃጢአት እንዳይሠራ ጻድቁን ብታስጠነቅቅ እርሱም ኃጢአት ባይሠራ፥ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን አድነሃል።” ሕዝ 3:17_21“ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም። በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው። ኃጢአትን አላደረግንም ብንል ሐሰተኛ እናደርገዋለን ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም።” 1 ዮሐ 1:8_10“ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ ወደ እናንተም ይቀርባል። እናንተ ኃጢአተኞች፥ እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ፥ ልባችሁን አጥሩ። ተጨነቁና እዘኑ አልቅሱም፤ ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወደ ትካዜ ይለወጥ። በጌታ ፊት ራሳችሁን አዋርዱ ከፍ ከፍም ያደርጋችኋል።” ያቆ4:8_10ማራናታ !!!

No comments:

Post a Comment